አሰር በአብዛኛዎቹ ምግቦቻችን (በተለይም የአትክልት ተዋጽዖዎች) በከፍተኛ መጠን የሚገኝ ግብዓት ነው ፤ ይህም በተፈጥሮው ለየት ያለ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር (carbohydrate) ሲሆን የሚለየውም ሰውነታችን እንደሌሎቹ ሁሉ በቀላሉ መፍጨት (digest ማድረግ) የማይችለው አይነት በመሆኑ ነው። ይህም ሆኖ ግን ሰውነታችን ዘወትር የሚፈልገው ንጥረ ነገር ነው ፤ ስለዚህ ዕለት ዕለት በቀላሉ በአመጋገባችን ውስጥ በማካተት ጤናችንን ልንጠብቅበት እንችላለን።
እያንዳንዱ ሰው በየዕለቱ ከ 25-35 ግራም አሰር በአመጋገቡ ውስጥ ማካተት ቢችል በቂ እንደሆነ ይታሰባል።
ይህ አሰር ለሰውነታችን እና ጤናችን ከሚሰጠን ጥቅሞች መካከል፦
• የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር
• የደም ውስጥ ስኳር መጠንን በጤናማ መጠን መጠበቅ
• የደም ቅባት መጠንን (cholesterol) በጤናማ መጠን በመጠበቅ የልብ የደም ሥር እንዲሁም ተያያዥ ሕመሞችን መከላከል
• ቶሎ ቶሎ የመራብ ስሜትን መከላከል
• የአንጀት ጤናን መጠበቅ
• የአጥንት ጤናን መጠበቅ (የካልሲየም absorption በማሻሻል) እና ሌሎችም ናቸው።
በዋናነት አሰር በምግቦቻችን ውስጥ በሁለት አይነት መንገድ ሊገኝ ይችላል ፤ ይህም የሚሟሟ (soluble fiber) እና የማይሟሟ (Insoluble fiber) ሲሆን ሁለቱም አይነት ለጤናችን እጅግ ጠቃሚ ናቸው፡፡
የሚሟሟ የአሰር አይነት እንደ ተልባ፣ አጃ፣ ፖም፣ ጥራጥሬዎች እና የቅባት እህሎች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በዋናነት የሚያገለግለን የደም ስኳር እና የደም ቅባት መጠንን ለመቆጣጠር ነው።
የማይሟሟ የአሰር አይነት ደግሞ በተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬዎች ፣ ጥራጥሬዎች እንዲሁም ያልተፈተጉ እህሎች ውስጥ የምናገኘው የአሰር አይነት ሲሆን በዋናነት የምግብ መፈጨት ስርዓትን ለማገዝ፣ የአንጀት ጤናን ለመጠበቅ እና የሆድ ድርቀትን ለመከላከል በከፍተኛ ሁኔታ ይጠቅመናል።
ማንኛውም ሰው ዕለት ዕለት በአመጋገቡ ውስጥ አስፈላጊ የአሰር መጠን ማካተት ያለበት ሲሆን በተለይ ደግሞ ክብደታቸውን መቀነስ፣ የደም ስኳር መጠናቸውን መቆጣጠር፣ የደም ግፊት እና ቅባት መጠናቸውን መቆጣጠር የሚፈልጉ ሰዎች እንዲሁም የመገጣጠሚያ ህመም የሚያጠቃቸው ሰዎች በልዩ ትኩረት አመጋገባቸው ውስጥ ሊያካትቱት ይገባል።
በቀን ውስጥ በቂ የአሰር መጠን ለማግኘት፡-
• በየዕለቱ በእያንዳንዱ የምግብ ሰዓት አትክልት እና ፍራፍሬን ማካተት
• የፍራፍሬ ጭማቂዎችን ከመጠቀም ይልቅ ሙሉ ፍራፍሬውን መመገብ
• እህሎችን መመገብ በሚያስፈልግ ጊዜ ሁሉ ያልተፈተጉ እህሎችን መምረጥ (ለምሳሌ ከፉርኖ ዱቄት ይልቅ ያልተፈተገ የስንዴ ዱቄት)
• 2 የሾርባ ማንኪያ ያህል ተቆልቶ የተፈጨ ተልባን በአመጋገብ ውስጥ ለማካተት መሞከር
• በተቻለ መጠን ጥራጥሬዎችን (ምስር፣ ሽምብራ፣ ባቄላ፣ ቦሎቄ ወዘተ) በአመጋገብ ውስጥ ማካተት
• በተቻለ መጠን የቅባት እህሎችን (ለውዝ፣ ተልባ፣ ሱፍ ወዘተ) በአመጋገብ ውስጥ ማካተት
• ሳይላጡ መበላት የሚችሉ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን ሁሉ በሚገባ በማጠብ ከነልጣጫቸው መመገብ ይጠቅማል።
ጤናማ ጊዜን ተመኘሁ!
ኬብሮን ሠናይ (የስነ ምግብ ሕክምና ባለሙያ)